Healthcare workers preparing for second strike
Updates
00
D
:
00
H
:
00
M
:
00
S
አሁንም ዶክተር መሆን ትፈልግ ይሆን?

አሁንም ዶክተር መሆን ትፈልግ ይሆን?

November 27, 2025
ከላይ የተቀመጠዉ ምስል ዶክተር መሆን የምትፈልግ የሶስት አመት ልጅ ጋወን በልክ ተሰርቶላት የአባቷን ስቴተስኮፕ ይዛ የተነሳችዉ ምስል ነዉ፡፡ የማወራችሁ ሰሞኑን በማርበርግ ወረርሽኝ ህይወት ለማዳን ሲጣጣር የተሰዋዉ የነርስ አማኑኤል ካሳ ልይህ ሴት ልጅ ስለ ሄመን አማኑኤል ነዉ፡፡ ስለአባት እና ልጅ ቅርበት ለማዉራት አልደፍርም ምክንያቱም ፎቶዉ ብዙ ይናገራል፡፡ ይልቁን ስለወንድሜ አማን ጥቂት ልናገር ለአራት አመታት ከአማን ጋር በሰራሁት ወቅት ያወኩት አንድ ነገር ቢኖር አማን ለሰዉ ልጅ እጅግ ግድ የሚሰጠዉ ሰዉ እንደሆነ ነዉ፡፡
በ 2015 የጂንካ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ክፍል ዳይሬክተር ሆኜ በተመደብኩበት ጊዜ አማን የቀዶ ህክምና ክፍል ነርሶች ሀላፊ ነበር፡፡ በዚህም ህይወቴን ካቀለሉልኝ ሰዎች የመጀመሪያዉ እና ብዙ ያስተማረኝ ሰዉ ነበር፡፡ ብዙ አስቸጋሪ ጊዜያትንም በመተሳሰብ አሳልፈናል፡፡ የክፍሉን ባለሙያዎች መብት ለማስከበርም ብዙ ታግለናል፡፡ ይህን በተመለከተ አንድ አሳዛኝ ታሪክ እዚህ ላይ ላንሳ፡፡
ለነርሶች የተጋላጭነት አበል 470 ብር እንዲከፈል የሚያዝ እና እየተተገበረ ያለ መመሪያ መኖሩ ለማንም ግልፅ ነዉ፡፡ ይህዉ መመሪያም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ በጂንካ ቀዶ ህክምና ክፍል ሲተገበር የነበረ ቢሆንም በ2014 ግን ሲከፈል የቆየዉ በስህተት እንጂ መመሪያዉ በግልፅ ለቀዶ ህክምና ነርሶች እንዲከፈል አያዝም በሚል ሰበብ በተመሳሳይ ክፍል(OR table) ላይ እየሰሩ ለጥቂቶች(surgical nurses) አየተከፈለ ለብዙሀን ነርሶች፤ ስክረብ እና ሰረኩሌት ነርሶች ጨምሮ እንዳይከፈል ተደረገ፡፡
ይህንን ኢፍትሀዊነትም አማን ብቻዉን(በጊዜዉ የሰራተኞች ተወካይ ስለነበርም) በሚፋለምበት ሰዓት ነበር አብረን መስራት የጀመርነዉ፡፡ ጉዳዩንም በሚገባ ካስረዳኝ በኁላ አብሬዉ ለመቆም ተስማማቼ ለሆስፒታል ስራ አስኪያጅ በተደጋጋሚ ደብዳቤ በማስገባትም በአካል በመሄድም፣ ለማኔጅመንት አባላት አሳዉቀን አጀንዳ ብናሲዝም፣ ለቦርድ እንዲቀርብ በተደጋጋሚ ጥረት አድርገን አጥጋቢ መልስ ባናገኝም ዞን ሲቪል ሰርቪስ እንዲሁም ክልል ጤና ቢሮ ድረስ ባለሙያ ተወካይ ብንልክም( ያን ጊዜ ጤና ቢሮ ሀዋሳ ነበር) ማንም መመሪያዉን አብራርቶ መልስ ሊሰጠን አልቻለም፡፡
በኋላም እኔ በስርዓቱ ተስፋ ቆርጬ በገዛ ፈቃዴ ሀላፊነት ለቅቄ በቀዶ ህክምና ክፍል በባለሙያነት እንዲሁም የሆስፒታሉ ሰራተኞች ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኜ ሳገለግል አማን የሆስፒታሉ የዲሲፒሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ ስለነበር በቅርበት እንሰራ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም የተረዳሁት አማን ምን ያህል ለእዉነት እና ለፍትህ ይቆረቆር እንደነበር ነዉ፡፡ የሆነዉ ሆኖ እኔ ሆስፒታሉን እስከለቀቅሁበት ጊዜ ማለትም ሚያዚያ 2017 ዓ.ም ድረስ አማን እና መሰሎቹ የተጋላጭነት አበል ሳይከፈላቸዉ እራሳቸዉን አጋልጠዉ ህዝብ በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡
የነርስ አማን ባለቤትም ዛሬ በቫይረሱ ምክንያት ህይወቷ ማለፉን እየሰማን ነው። እጅግ በጣም ያሳዝናል።
ወደ ጥያቄዉ ስመለስ ይህን ኢፍትሀዊነት ያየችዉ እና ተጋላጭነትህን አላዉቅልህም ላለዉ ህዝብ እና መንግስት እራሱን እና ቤተሰቡን አጋልጦ ሲያክም ለህልፈት የተጋለጠዉን አባቷዋን ህይወት የተመለከተችዉ ሄመን አማን አሁንም ሀኪም መሆን ትፍልግ ይሆን? ልጆቻቸውን ሜዳ ላይ በትነው ሄዱ። ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማርልን። ፌደራል መንግስት እና የክልሉ መንግስት ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን በሙሉ እንዲያደርጉላቸው እናሳስባለን። Dr DRRD
💥እኛ የጤና ባለሞያዎችም ለልጆቹ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ልንረባረብ ይገባል።
ይህን የጤና ባለሙያ ህይወት ከምንም የማይቆጥር ስርዓት መታገል ለነገ የማይባል ስራችን ሊሆን ይገባል። ከማለቃችን በፊት ታህሳስ 6 ለሚጀምረው የስራ ማቆም አድማ ሁላችንም እንዘጋጅ‼️ ይበቃል‼️